የአሁኑ ክፍል ::ሞዴል
ትምህርት በመጻሕፍት ማመን
አላህ (ሱ.ወ) በመልክተኞቹ ላይ ወደ ባሮቹ ያወረዳቸው መጽሐፍት እንዳለው፣ እነኚህ መጽሐፍት በሙሉ የአላህ ቃልና ንግግር እንደሆኑ ማመን ነው፡፡ ለክብርና ልቅናው ተገቢ በሆነ መልኩ በርግጥ ተናግሯል፡፡ እነኚህ መጽሐፍት በውስጣቸው ለሰው ልጅ፣ ለሁለቱም ዓለም ሚሆን መመሪያና ብርሃን የያዙ እውነቶች ናቸው ማለትን በቁርጠኝነት ማረጋገጥ፡፡
በመጽሐፍት የማመን አንገብጋብነት
በመጽሐፍት ማመን ከኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱማዕዘን ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው፣ በዚያም በመልክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍ፣ በዚያም ከበፊቱ ባወረደው መጽሐፍ እመኑ፡፡» (አል ኒሳእ 136) አላህ (ሱ.ወ) በርሱ በመልዕክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍ፣ በቁርኣን እንድናምን አዟል፡፡ ከቁርኣን በፊት በተወረዱ መጽሐፍት ማመንን አዟል፡፡
ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ኢማንን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፡ - «በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመጽሐፍቱ፣ በመልዕክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀንና በክፉም በደጉም በአላህ ውሳኔ ልታምን ነው፡፡» (ሙስሊም 8)
በመጽሕፍት ማመን ምንን ያካትታል?
በቀደምት መጽሐፍት ውስጥ ስላለ ነገር ሊኖረን የሚገባ አቋም ምንድን ነው?
አንድ ሙስሊም፣ በነብዩላህ ሙሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው ተውራት፣ በነብዩላህ ዒሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው ኢንጂል፣ በትክክል ከአላህ ዘንድ የተወረዱ እንደነበሩ ያምናል፡፡ ሁለቱም በውስጣቸው ለሰው ልጆች ለዚች ዓለምና ለወዲያኛው ዓለም ሕይወታቸው መመሪያና ብርሃን የያዙ፣ ተግሳጻትን እንዲሁም ድንጋጌዎችንና ዜናዎችን አቅፈው የነበሩ መሆናቸውን ያምናል፡፡ ነገር ግን አላህ (ሱ.ወ) በቁርኣን ውስጥ የመጽሐፍት ባለቤት የሆኑት አይሁዶችና ክርስቲያኖች፣ መጽሐፍታቸውን እንደበረዙና እንዳበላሹ፣ ከመጽሐፍ ያልሆነን ነገር በውስጡ እንደጨመሩ፣ ከነበረውም እንደቀነሱ ነግሮናል፡፡ በመሆኑም በወረዱበት ይዘት ላይ አልቆዩም፡፡
አሁን ያለው ተውራት፣ በሙሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው ተውራት አይደለም፡፡ ምክንያቱም አይሁዶች አጣመውታል፤ ለውጠውታል፡፡ በርካታ ድንጋጌዎቹን ተጫውተውበታል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከነዚያ አይሁዳውያን ከሆኑት ሰዎች ንግግሮችን ከስፍራዎቹ የሚያጣምሙ አሉ፡፡» (አል ኒሳእ 46)
አሁን ያለው ኢንጂልም ቢሆን በዒሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው ኢንጂል አይደለም፡፡ ክርስቲያኖችም ኢንጂልን አጣመውታል፡፡ በርካታ በውስጡ የነበሩ ድንጋጌዎችን ለውጠዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ክርስቲያኖችን በማስመለከት እንዲህ ብሏል፡- «ከነሱም እርሱ ከመጽሐፉ ያላደለ ሲኾን ከመጽሐፉ መኾኑን እንድታስቡ በመጽሐፉ ምላሶቻቸውን የሚያጣምሙ ክፍሎች አሉ፡፡ እርሱ ከአላህ ዘንድ ያልኾነ ሲኾን እርሱ ከአላህ ዘንድ ነውም ይላሉ፡፡ እነርሱ የሚያውቁ ሲኾኑም በአላህ ላይ ውሸትን ይናገራሉ፡፡» (አለ ዒምራን 78)
«ከነዚያም እኛ ክርስቲያኖች ነን ካሉት የጠበቀ ቃል ኪዳናቸውን ያዝን፡፡ በርሱም ከታዘዙበት ነገር ፈንታን ተዉ፤ ስለዚህ እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ በመካከላቸው ጠብንና ጥላቻን ጣልንባቸው አላህም ይሰሩት የነበሩትን ሁሉ በእርግጥ ይነግራቸዋል፡፡» (አል ማኢዳ 14) ዛሬ በመጽሐፍት ባለቤቶች እጅ የሚገኘው፣ ተውራትንና ኢንጂልን አካቷል ብለው የሚያምኑበት መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ በርካታ ብለሹ የእምነት አመለካከቶችንና ትክክለኛ ያልሆኑ ዜናዎችን፣ እንዲሁም የውሸት ትረካዎችን ይዟል፡፡ ስለሆነም ከዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቁርኣን ወይም ትክክለኛ የሐዲስ ዘገባ እውነትነቱን ያጸደቀውን በስተቀር እውነት ብለን አናምንበትም፡፡ ቁርኣንና ሀዲስ ያስተባበሉትንደግሞ እናስተባብላለን፡፡ ከዚህ ውጭ የሆነውን በዝምታ እናልፋለን፡፡ እውነት ብለን አናጸድቅም ውሸት ነው ብለንም አናስተባብልም፡፡
አሁን ያለው ተውራት፣ኢንጂል ሰዎች አጣመውታል፤ለውጠውታል ብለን ቁርኣን እንደ ነገረን እናምናለን፤ እንዲህ ከመሆኑም ጋራ፣ አንድ ሙስሊም እነኚህን መጽሐፍት አያንኳስስም፤ አያራክስም፣ ምክንያቱም ምናልባት በውስጣቸው ያልተበረዘና ያልተለወጠ የአላህ ንግግር ቅሪት ሊኖር ይችላል፡፡
ቁርኣንን አስመልክቶ ያለብን ግዴታ ምንድን ነው?
እመት ዓኢሻ(ረ.ዐ)፣ ስለ ነብዩ (ስ.ዐ.ወ) ባህሪ በተጠየቁ ጊዜ፣ «ባህሪያቸው ቁርዓን ነበር፡፡ « በማለት መልሰዋል፡፡ (አህመድ 24601/ሙስሊም 746)
የሐዲሱ መልክት፣ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ)፣ በኑሯቸውና በተግባራቸው የቁርዓንን ድንጋጌና ሕግጋት በመፈፀም የሚያሳዩ እንደነበሩ ይገልጻል፡፡ በርግጥም ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለቁርኣን መመሪያ ሙሉዕ ተከታይነታቸውን አስመስክረዋል፡፡ እሳቸው ለእያንዳንዳችን ዓይነተኛ ተምሳሌታችን ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ለናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለኾነ ሰው አላህንም በብዙ ለሚያወሳ፣ በአላህ መልክተኛ መልካም መከተል አላችሁ፡፡» (አል አህዛብ 21)
mmm
የቁርኣን ልዩ መገለጫዎች
የተከበረው ቁርኣን በነብያችንና በአርአያችን በሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ላይ የተወረደ የአላህ ቃል ነው፡፡ በመሆኑም ሙእሚን ይህን” መጽሐፍ በእጅጉ ያልቀዋል፡፡ ድንጋጌዎቹን ለመተግበርና አንቀፆቹን እያስተነተነ ለማንበብ ይጥራል፡፡ ይህ ቁርኣን በቅርቢቱ ዓለም መመሪያችን፣ በመጨረሻው ዓለም የስኬታችን ሰበብ መሆኑ ብቻ ልዩ ለመሆን ይበቃዋል፡፡ የተከበረው ቁርኣን በርካታ መለያዎች አሉት፡፡ ከቀደሙት መለኮታዊ መጽሐፍት የሚነጥሉት የርሱ ብቻ የሆኑ የተለያዩ መገለጫዎችም አሉት፡፡ ከነኚህም መካከል፡-
1 የተከበረው ቁርኣን የአምላክን ድንጋጌ ማጠቃለያ የያዘ መሆኑ፡፡
የተከበረው ቁርኣን በቀደምት መጽሐፍት ውስጥ ያለውን፣ አላህን በብቸኝነት የመገዛት ትዕዛዝን የሚያጠናክር ኾኖ ነው የመጣው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ወደ አንተም መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭና በርሱ ላይ ተጠባባቂ ሲኾን በውነት አወረድን» (አል ማኢዳ 48)«ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭ» ማለት በቀደምት መጽሐፍት ውስጥ ከተነገሩ ዜናዎች፣ ከተላለፉ የእምነት አመለካከቶችና ጉዳዮች ጋር የሚስማማና የማይቃረን ማለት ነው፡፡ «በርሱ ላይ ተጠባባቂ» የሚለው ደግሞ ከርሱ በፊት የነበሩ መጽሐት ላይ የሚመሰክርና በአደራ የሚጠብቅ ማለት ነው፡፡
2 እነሆ የሰው ልጆች በሙሉ በቋንቋና በጎሳ መለያየታቸው እንዳለ ሆኖ እርሱን የመከተል ግዴታ አለባቸው፡፡
እነሆ የሰው ልጆች በሙሉ ፣ ዘመናቸው ምንም እንኳ ከቁርኣን መወረድ በኋላ የመጣ ቢሆንም እርሱን የመከተል፣ እርሱ ያቀፈውን የመተግበር ግዴታ አለባቸው፡፡ ቀደምት መጽሐፍት ግን የተወረዱት ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ለተወሰኑ ሕዝቦችና በተወሰነ ዘመን ላይ ነበር፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ይህም ቁርኣን እናንተንና የደረሰውን ሰው ሁሉ በርሱ ላስፈራራበት ወደኔ ተወረደ (በል)፡፡» (አል አንዓም 19)
3 አላህ (ሱ.ወ) የተከበረውን ቁርኣን የመጠበቁን ኃላፊነት ለራሱ አድርጎታል፡፡
በመሆኑም የመቀየር፣ የመደለዝ፣ የመከለስና የመበረዝ እጅ አልተሰነዘረበትም፡፡ ወደፊትም ለመቼውም አይዘረጋበትም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፤ እኛም ለርሱ ጠባቂዎቹ ነን፡፡» (አል ሒጅር 9) ሰለሆነም በውስጡ ያሉ ዜናዎች በሙሉ ትክክለኛ ናቸው፡፡ ልንቀበለውም የግድ ይላል፡፡