የአሁኑ ክፍል ::ሞዴል
ትምህርት የኢድ አልፈጥር እና የኢድ አል-አድሃ አረፋ በዓል
የጾም ፍቺ በዓል
የጾም ፍቺ በዓል፣ የረመዳን የመጨረሻው ሌሊት ካለፈ በኋላ የሚከተለው የወርሃ ሸዋል የመጀመሪያው ቀን ነው፡፡ የጾም ፍቺ በዓል በመባል የሚጠራውም ለዚህ ነው፡፡ ይህ ቀን፣ ሰዎች ጾማቸውን በማጠናቀቃቸው፣ በጾማቸው አላህን ይገዙበት እንደነበረው፣ በመደሰት አላህን የሚያመሰግኑበት ዕለት ነው፡፡ ሙስሊሞች ይህን በዓል የሚያከብሩት፣ አላህ ጸጋውን ስላሟላላቸውና የረመዳንን ወር በሙሉ ለመጾም ስላደላቸው፣ አላህን እያመሰገኑ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ቁጥሮችንም ልትሞሉ አላህንም ቅኑን መንገድ ስለመራችሁ ታከብሩትና ታመሰግኑት ዘንድ (ይህን ደነገግንላችሁ)›› (አል በቀራ 185)
በኢስላማዊው ሕግ የተደነገጉና በጾም ፍቺ ዒድ ዕለት የሚከናወኑ ነገሮች እንዴት ያሉት ናቸው?
የጾም ፍች ምጽዋት(ዘካተል ፊጥር)፡ አላህ (ሱ.ወ) በዒድ ዕለት፣ ቀንና ሌሊቱን ከሚበላው የሚተርፍ ነገር ያለው ሰው አገሬው ከሚመገበው ሩዝ ወይም ስንዴ ወይም ተምር አንድ ቁና ለሙስሊም ድሆችና ችግረኞች እንዲሰጥ ግዴታ አድርጓል፡፡ ይህም ድሆችና ችግረኞች በዒድ ዕለት ተቸግረው እንዳይውሉ ያደርጋቸዋል፡፡
የዘካተል ፊጥር መስጫ ጊዜ፡ የመጨረሻው የረመዳን ቀን ፀሐይ ከጠለቀችበት ሰዓት ጀምሮ፣ የዒድ ሠላት እስከሚሰገድበት ወቅት ድረስ ነው፡፡ ከዒዱ አንድ ወይም ሁለት ሌሊት ቀደም ብሎ መስጠትም ይቻላል፡፡
ዓይነትና መጠኑ፡ ከሀገሬው ምግብ የሆነ አንድ ቁና ሩዝ ወይም ተምርና የመሳሰሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ቁና የመስፈሪያ ልክ ነው፡፡ ነገር ግን በዘመናዊ የሚዛን ልኬት መሆኑ የተሻለ ነው፡፡ በግምት ሦስት ኪሎግራም ይሆናል፡፡
ለራሱ፣ ለሚስቱ ልጆቹ፣ እንዲሁም ቀለብ ለሚሰፍርላቸውና ለሚያስተዳድራቸው ሰዎች የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ በእናቱ ማህፀን ውስጥ ላለ ፅንስ ማውጣትም ይወደዳል፡፡ ለእያንዳንዱ ሰው ካገሬው ምግብ አንድ ቁና ይወጣለታል፡፡
ምጽዋቱ ዘካህ ጥበብ
ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ይህን ሲደነግጉ፣ ምጽዋቱ፣ ጾመኛ በማላገጥና በመጫወት ምክንያት የሚያገኘውን ወንጀል እንዲያብስለተና ለችግረኞች ቀለብ ይሆን ዘንድ ነው፡፡ ከሠላት በፊት ላደረሳት፣ ተቀባይነት ያላት ምጽዋት ትሆናለች፡፡ ከሠላት በኋላ ላደረሳት ደግሞ እንደማንኛውም ሠደቃ፣ ሠደቃ ነች ብለን እንወስደዋለን፡፡ (አቡ ዳውድ 1607)
ዒድ አልአድሓ፣ በወርሃ ዙልሒጃ አስረኛ ቀን ላይ የሚከበር ሁለተኛው የሙስሊሞች በዓል ነው፡፡ ይህ ወር በኢስላማዊው ቀመር አስራ ሁለተኛው ወር ነው፡፡ በዚህ ዕለት በርካታ ትሩፋቶች ይገኛሉ፡፡ ከነኚህም ትሩፋቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
1 የዒድ አልአድሓ ቀን ከዓመቱ ቀናት ሁሉ በላጩ ቀን ነው
የዒድ አልአድሓ ቀን ከዓመቱ ቀናት ሁሉ በላጩ ቀን ነው፡፡ ከዓመቱ ቀናት በሙሉ በላጮቹ ቀናት የወርሃ ዙልሂጃ የመጀመሪያዎቹ አስር ቀናቶች ናቸው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡-‹‹ከነዚህ አስርት ቀናት ይበልጥ አላህ ዘንድ በውስጣቸው የሚሠሩ መልካም ሥራዎች ተወዳጅ የሚሆኑበት ቀን የለም፡፡›› ብለው ሲናገሩ ባልደረቦቻቸው፣ «በአላህ መንገድ ላይ የሚደረግ ትግልም ቢሆን?» በማለት ጠየቁ፤ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹አዎን! ነፍሱንና ንብረቱን ይዞ የወጣ፣ ከዚያም አንዱንም ይዞ ያልተመለሰ ሰው ካልሆነ በስተቀር፣ በአላህ መንገድ ላይ የሚደረግ ትግልም ቢሆን (አይበልጥም) አሉ፡፡ (አል ቡኻሪ 926 / አት ቲርሚዚ 757)
የታላቁ ሐጅ ዕለት ነው፡ በውስጡ ከሐጅ ሥራዎች እጅግ የላቀው፣ አንገብጋቢውና የተከበረው ሥራ ይገኛል፡፡ ያም፣ በካዕባ ዙሪያ መዞር፤ እርድን መፈፀም፤ ጀምረተል ዐቀባ ላይ ጠጠር መወርወርና ሌሎች ተግባራት የከናወኑበታል፡፡
በእርዱ ቀን(የውመ ነሕር) የሚሠሩ ሥራዎች
ሐጅ ላይ ላልሆነ ሰው፣ በዒድ አልአድሓ ዕለት ከዘካተል ፊጥር ውጭ በጾም ፍች በዓል ላይ የሚተገበሩ ነገሮችን በሙሉ መተግበር ይፈቀድለታል፡፡ ዘካተል ፊጥር(የጾም ፍች ምጽዋት)፣ በጾም ፍቺ በዓል ላይ ብቻ የሚተገበር ነው፡፡ የእርድ በዓል (ዒድ አልአድሓ)፣ ወደ አላህ መቃረቢያ እርድ (ቁርባን) የሚቀርብበት ዕለት መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡
እርድ(ኡዱሒያ)፡ እርድ(ኡዱሒያ)፣ በእርድ ቀን ከዒድ ሠላት መልስ ወደ አላህ ለመቃረብ የሚሰዋ ወይም የሚታረድ ግመል፣ ከብት፣ ወይም ፍየልና በግ ሲሆን የወርሃ ዙል ሒጃ አስራ ሦስተኛ ቀን ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ሊተገበር ይችላል፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ስለዚህ ለጌታህ ስገድ (በስሙ) ሰዋም፡፡›› (አል ከውሰር 2) አንቀጹ በዒድ ሠላትና በዒድ ዕለት በሚፈፀሙ እርዶች ተተርጉሟል፡፡
የ እርድ ብያኔ
ኢስላማዊ ፍርዱ፡ እርድ፣ በሚችል ሰው ላይ ጠበቅ ያለ ሱና ነው፡፡ አንድ ሙስሊም ለራሱና ለቤተሰቦቹ ማረድ አለበት፡፡
ለማረድ ያቀደ ሰው ከወርሃ ዙልሒጃ የመጀመሪያ ዕለት ጀምሮ እርዱን እስኪፈጽም ድረስ፣ ፀጉሩን መላጨት፣ ጥፍሩንም መቁረጥ የለበትም፡፡
ለእርድ የሚቀርበው እንሰሳ ማሟላት ያለበት መስፈርት
ከቤት እንሰሳት መሆን አለበት፡፡ እነሱም፡- ፍየል፣ በግ፣ ከብትና ግመል ናቸው፡፡ ከነዚህ ሌላ ያሉ እንሰሳት ወይም በራሪ አዕዋፋት ለእርድ አይቀርቡም፡፡ አንድ ፍየል ወይም በግ ለአንድ አባወራ ከነቤተሰቡ ይበቃዋል፡፡ በአንድ በሬ (ላም) ወይም ግመል ላይ ሰባት አባወራ ሊሳተፍ ይችላል፡፡
የሚፈለግበት የዕድሜ ገደብ ላይ የደረሰ መሆን አለበት፡፡
የሚፈለገው የዕድሜ ገደብ፡- ለበግ ስድስት ወር፤ ለፍየል አንድ ዓመት፤ ለበሬ(ላም) ሁለት ዓመት፤ እና ለግመል አምስት ዓመት ነው፡፡
እንሰሳው ግልጽ ከወጣ ነውርና ጉድለት የጸዳ መሆን አለበት
እንሰሳው ግልጽ ከወጣ ነውርና ጉድለት የጸዳ መሆን አለበት፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አራት ዓየነት እንሰሳት ለእርድ ብቁ አይደሉም፡- ጠንጋራነቷ ግልጽ የሆነ እንሰሳ፤ ህመሟ ይፋ የሆነ እንሰሳ፤ አንካሳነቷ ግልጽ የሆነ እንሰሳ እና መረቅ የማይወጣት በጣም የከሳች እንሰሳ ›› (አል ነሳኢ 4371 አት ቲርሚዚ 1497)