የአሁኑ ክፍል ::ሞዴል
ትምህርት ትምህርት፡ የጉዞ ሽርሽር እና ንፅህና
አንድ ሰው በጉዞ ላይ በሚቆይበት ቦታ የሚፈጠሩ ከስተቶች እና በዙሪያው ባሉ ነገሮች ምክኒያት የሰውየው ባህሪ ይለዋወጣል። አቡ ኹረይራ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፈው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡ ‹‹ጉዞ የመከራ ቁራጭ ነው አንዳችሁን ምግቡን መጠጡን እንቅልፉን ይከለክለዋል›› (አል-ቡኻሪ 1804 ፣ 3001 ፣ 5429 እና ሙስሊም 1927) ጉዞና ጉብኝት የሚያደርጉ ሰዎች ከንፅህና እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የተወሰኑ ነገሮችን ማዎቅ አለባቸው። ከእነዚህም ውስጥ
እንደ ጥላ ፣ ዛፎች ወይም ሌሎች ለማረፊያነት የተከለሉ ቦታዎችን መበከል እና በእነዚህ ቦታ ላይ መፀዳዳት የተከለከለ ነው።
ተጓዙ በረባዳማ (በሜዳ ፣ በጫካ) ቦታ ውስጥ ከሆነና መፀዳዳት ከፈለገ ለስላሳ ቦታ መፈለግ ተመራጭ ነው ሲሉ ሊቃውንት ይናገራሉ። ከሽንት ብክለት ለመዳን እና ሽንቱ ወደ እራሱ ተመልሶ እንዳይረጨው፤ ከደረቅ መሬት እና ከሚነፍስ ንፋስ መራቅ አለበት።
2 በሚፅዳዱ ጊዜ ሃፍረተ ገላን መሸፋፈን
ሲፅዳዱ ከሰዎች ዕይታ ለመራቅ መሸፋፈኑ ግዴታ ነው። ለዚህም መከለያ ነገር መጠቀም ወይም ከሰዎች ራቅ ብሎ መሄድ ያስፈልጋል። በሙጊራ ኢብን ሹዕባ ሐዲስ መሰረት እንዲህ አለ፡ በአንድ ጉዞ ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር እየተጓዝን እያለ ‹‹ሙጊራ ሆይ! ይህን የውሃ እቃ ያዝ›› አሉኝ። ያዝኩ፤ የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እስኪጠፉኝ ድረስ ራቅ ብለው ሄዱ። ለተፈጥሮ ጥሪ መልስ ሰጡ።›› (ቡኻሪ 363 ፣ ሙስሊም 274) በሌላ ሐዲስ ደግሞ ‹‹ጉዳያቸውን ሊፈፅሙ (ሊጥራሩ) ከሆነ ራቅ ብለው ይሄዳሉ።›› (ሙሰነድ ኢማሙ አህመድ 15660)
በአብዱሏህ ኢብን ጃዕፈር (ረ.ዐ) ሐዲስ ውስጥ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ‹‹የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ለተፈጥሮ ጥሪ መልስ ለመስጠት ደባቃ ቦታ ወይም የተምር ዛፎች ክምችትን ይወዱ ነበር።›› (ሙስሊም 342) በሌላ ሐዲስ እንደተገለፀው ደግሞ፡ ‹‹ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጉዳያቸውን ሊያስታግሱ ሲፈልጉ ልብሳቸውን ከፍ አያደርጉትም፤ እንዲያውም ልብሳቸው ከመሬቱ ጋር ይገጥም ነበር።›› (አቡዳውድ 14) ለዚህ ምክኒያቱ መሸሸግ እና ከሰው እይታ መራቅ ነው።
ተየሙም ሶላት ለመስገድ ውሃ በሌለ ጊዜ ወይም (በህመም ምክኒያት) ውሃን ለመጠቀም ባልተቻለ ጊዜ የሚደረግ አንዱ የንፅና ዘዴ ነው። የሚደረገውም፡ ሙስሊም ሰው መሬቱን በእጆቹ መታመታ ያደርጋል፤ ከዚያም በእጆቹ ፊቱን ያብሳል። በማስከተልም በግራ እጁ ቀኝ እጁን፤ በቀኝ እጁ ደግሞ የግራ እጁን ያብሳል ማለት ነው።
ለአንድ ሙስሊም ሰው በብዙ ምክኒያቶች በአካባቢው ተረጋግቶ ከሚኖር ሰው በላይ በጉዞ ላይ ያለ ሰው ተየሙም ያስፈልገዋል። ለምሳሌ ሙሉ በሙሉ ውሃ ከሌለ ወይም የውሃ እጥረት በመኖሩ ለመጠጥ እና ለምግብ ብቻ የሚሆን ከሆነ እና በሌሎች መሰል ምክኒያቶች ነው።
ወይም ደግሞ በውሃ ውዱዕ (ከፊል ትጥበት) በማድረጉ የሚደርስበት ጉዳት ካለ ፣ (የበሽታ መባባስ) በከባድ ብርድ ምክኒያት ሲሆን ይህ ብዙ ጊዜ በጉዞ ወቅት ይከሰታል። ብርድ ተብሎ የተጠቀሰው እታመማለሁ ወይም በጣም ያስፈራኛል ብሎ ካሰበ ለሰውየው በጣም አስቸጋሪ የሚሆንበት ከሆነ ማለት ነው። ነገርግን የተለመደው ቅዝቃዜ ለዚህ ምክኒያት አይሆንም።
ውሃ የለሆኖ በአቅራቢውም ማምጣት ካልተቻለ ወይም ብርዳማ ሆኖ ማሞቅ ካልተቻለ ተየሙም ማድረጉ መሽሩዕ (የተፈቀደ ህጋዊ) ነው።
ኹፍ (ካልስ) ላይ ማበስ፡ እንደ ካልሲ ጥልቅ የሚል ሆኖ እግርን የሚሸፍን ከቆዳ የተሰሩ ጫማዎች ወይም ካልሲዎች ወይም ደግሞ መሰል ነገሮች ላይ ሲሆን ንፁህ ሆኖ ሙሉ እግርን የሚሸፍን እና ከትንሹ እና ከትልቁ ሐደስ (ብክለት-ንፅህና ጉድለት) የጠራ ከሆነ ነው። የላይኛውን የእግሩን ክፍል ካልሲው (ሁፉ) ላይ ማበስ ነው።
በሁፍ (ካልሲዎች) ላይ ለማበስ ቅድመ ሁኔታዎቹ ንፁህ መሆን ፣ እግርን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍኑ ፣ የለበሳቸው ሰው ውዱዕ ካደረገ በኋላ እግሩን ታጥቦ ከሆነ የሚሉት ናቸው። እነዚህን ካሟላ በእነሱ ላይ ማበስ ይችላል። ነዋሪ ከሆነ ለአንድ ቀን እና ለአንድ ሌሊት፤ ተጓዥ ከሆነ ደግሞ ለሶስት ቀን እና ለሶስት ሌሊት እንደለበሳቸው መቀጠል ይችላል።
የማበሻ ጊዜው ካበቃ በኋላ ውዱዕ ማድረግ ቢፈልግ ካልሲዎቹን ማውለቅ አለበት። ወይም ደግሞ በንፅህና ጉድለት እና መሰል ነገሮች ጉሱል (ገላውን) መታጠብ ቢኖርበት ፣ ያለ ንፅህና ለብሷቸው ከሆነ እግሩንም በማጠብ እራሱን ሙሉ በሙሉ ያነፃል።