የአሁኑ ክፍል ::ሞዴል
ትምህርት ውዱእ ማድረግ
የውዱእ ትሩፋት
ውዱእና ከነጃሳ መጸዳዳት፣ ትሩፋት የሚያስገኙና የላቁ ተግባራት ናቸው፡፡ አንድ ባሪያ ዓላማውን ካሳመረና ለአላህ ካጠራ፣ እንዲሁም ከአላህ ምንዳን ከከጀለበት፣ አላህ በርሱ ወንጀሉንና ስህተቱን ያብስለታል፡፡ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ)፡ -«አንድ ሙስሊም ውዱእ በሚያደርግበት ጊዜ፡ ፊቱን ሲታጠብ፣ በዓይኑ በመመልከት የሰራው የእይታ ወንጀል ከውሃው ጋር ከፊቱ ይወገዳል፡፡ እጁን ሲታጠብ፣ በእጁ የፈፀመው ወንጀል ከውሃው ጋር ይወገዳል፡፡ እግሮቹን ሲያጥብ፣ በእግሮቹ በመጓዝ የፈፀመው ወንጀል ከውሃው ጋር ከእግሮቹ ይወገዳል፡፡ በዚህ መልኩ ከወንጀል ጽዱዕ ሆኖ ይወጣል፡፡» ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 244)
ውዱዕ የማደርገውና ትንሹን ሐደስ የማስወግደው እንዴት ነው?
በልብ ማሰብ (ኒያ)
አንድ ሙሰሊም ውዱእ ማድረግ በሚፈልግ ጊዜ ውዱዕ ማድረጉን ሊያስብ ይገባል፡፡ ይኸውም በልቦናው ሐደስን እንደሚያስወግድ ማሰብ ነው፡፡ በልብ ማሰብ (ኒያ) ለማንኛውም ተግባር ተቀባይነት መስፈርት ነው፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ)፡ - «ስራዎች የሚለኩት እንደ ታሰበላቸው ዓላማ ነው፡፡» ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 1/ ሙስሊም 1907) ከዚያም በሚከተለው ቅደም ተከተል መሰረት እንዲሁም በማዕዘናቱ መሐከል ረዥም ቆይታ ሳይኖር ወዱእ ማድረግ ይጀምራል፡፡
መዳፎቹን ሶስት ጊዜ ይታጠባል፡፡ ይህ የተወደደ ተግባር(ሙስተሐብ) ነው፡፡
በውሃ ይጉመጠመጣል፡፡ ይኸውም በአፉ ውስጥ ውሃን በማስገባትና ተግሞጥሙጦ በመትፋት ይሆናል፡፡ ይህን ሶስት ጊዜ ቢያደርግ የተወደደ ነው፡፡ ግዴታው ግን አንድ ጊዜ ማድረግ ነው፡፡
ይሰረነቃል፡፡ ይኸውም ውሃን በአፍንጫው በመሳብ ከዚያም በአፍንጫ ገፈቶ ማውጣት ነው፡፡ ውሃውን የሚያስወጣው በአፍንጫው በሚያስወጣው አየር ነው፡፡ በርሱ ላይ ጉዳት ከሌለው በስተቀር ውሃን በሚገባ ወደ ውስጥ መሳብ (መሰርነቅ) የተወደደ ነው፡፡ ሶስት ጊዜ ይህን ማድረግ ምስተሐብ ነው፡፡ ግዴታው ግን አንድ ጊዜ ብቻ ነው ፡፡
ፊቱን ይታጠባል፡፡ የግንባሩ፣ ከፀጉር መብቀያው ጫፍ እስከ አገጩ ስር ድረስ፣እንዲሁም ከአንዱ ጆሮ እስከ ሌላኛው ጆሮ ድረስ በመታጠብ የሚፈፀም ነው፡፡ ይህንንም ሶስት ጊዜ ቢፈፅም የተወደደ ነው፡፡ ግዴታው ግን አንድ ግዜ ብቻ ነው፡፡ ጆሮዎች የፊት አካል አይደሉም፡፡
እጆቹን ከጣቶቹ ጫፍ እስከ ክርኑ ድረስ ያጥባል፡፡ክርኖች በትጥበቱ ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ሶስት ጊዜ መደጋገሙ ይወደዳል፡፡ ግዴታው አንድ ግዜ ብቻ ነው፡፡
እራሱን(ፀጉሩን) ያብሳል፡፡ ይኸውም መዳፎቹን በውሃ በማራስ፣ ከግንባሩ በመጀመር፣ ከማጅራቱ ቀጥሎ እስከለው የኋለኛው የራስ ጫፍ ድረስ ማባስ ነው፡፡ በመዳፎቹ እያበሰ ወደ ፊትለፊት መመለሱ ይወደዳል፡፡ እንደሌሎቹ የሰውነት ክፍሎች ሶስት ጊዜ መደጋገም የተወደደ አይደለም፡፡
ጆሮዎቹን ያብሳል፡፡ ይኸውም ጭንቅላቱን ካበሰ በኋላ ሁለቱን አመልካች ጣቶቹን ጆሮዎቹ ውስጥ በማስገባት በአውራጣቱ ደግሞ የላይኛውን የጆሮው ክፍል ማበስ ነው፡፡
እግሮቹን ከነቁርጭምጭሚቶቹ ያጥባል፡፡ ሶስት ጊዜ ደጋግሞ ማድረጉ የተወደደ ነው፡፡ ግዴታው ግን አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ካልሲ ከለበሰ መስፈርቶቹን ጠብቆ በላዩ ላይ ማበስ ይችላል፡፡