የአሁኑ ክፍል ::ሞዴል
ትምህርት ባል እና ሚስት ለመምረጥ ሊከተላቸው የሚገቡ መርሆዎች
የጋብቻ ትሥሥር በእስልምና ውስጥ በጣም ጠቃሚ እና ትልቅ ዋጋ ካላቸው ውሎች መካከል አንዱ ነው። የእስልምና ህግ ሁለቱ ጥንዶች ፍላጎቶቻቸውን የሚያሳኩበት እና ከውሉ የሚጠቀሙበትን የዝግጅት ደረጃዎች አስቀምጧል። እንዲሁም ትዳሩ እንዲቀጥል እና የሙስሊም ቤተሰብ መረጋጋት ያለው ይሆን ዘንድ የራሱ ሚና አለው።
ቤተሰብ የሚመሰረትባቸው ሁለቱ ዋና ምሰሶዎች ባል እና ሚስት ናቸው። በእነሱ መካከል ጥሩ ግኙኝነት እንዲኖር ሸሪአ አፅንኦት ይሰጣል። ይህም አሏህ በባሮቹ ላይ ካደረጋቸው ምልክቶች እና ፀጋዎች ውስጥ አንዱ ነው።
አሏህ እንዲህ አለ፡ "ለእናንተ ከነፍሶቻችሁ ሚስቶችን ወደ እነሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ ፣ በመካከላችሁም ፍቅርን እና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶች ነው። በዚህ ውስጥ ለሚያስተውሉ ህዝቦች ተአምራቶች አሉ።" (ሱረቱ ሩም 21)
የትዳር አጋር ምርጫን ማሳመር
የትዳር የህይወት አጋርን አሳምሮ መምረጥ የመልካም ጋብቻ ና የጠንካራ ቤተሰብ መመስረት ወሳኝ እርምጃ ነው
ጥሩ የትዳር የህይወት አጋር ለመምረጥ የሚያስፈልጉ ጠቃሚ መስፈርቶች
ሁሉም ወንዶች እና ሴቶች የህይወት አጋራቸውን በሚመርጡበት ጊዜ በአሏህ ፈቃድ በሁለቱም ሐገር ደስታን ለማግኘት መሰረታዊ መስፈርታቸው ሊሆን የሚገባው ሃይማኖቱን አጥብቆ የያዘ እና ጥሩ ስነ-ምግባር ወይም ባህሪ ያለው የሚለው ነው።
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጥሩ ሃይማኖተኛ ሴትን ለትዳር መምረጥ እንደሚገባ አስተምረዋል። እንዲህ አሉ፡ ‹‹አንዲት ሴት ለአራት ነገሮች ትገባለች። ለገንዘቧ ፣ ለዘሯ ፣ ለውበቷ (ለመልኳ) እና ለሃይማኖቷ ናቸው። ሆኖም ሃየማኖተኛን ሴት አግቡ፤ ያለበለዚያ እጃችሁ አመድ አፋሽ ይሆናልና።›› (ቡኻሪ 5090 ፣ ሙስሊም 1466) በእርግጥ ሃይማኖተኛ ሴት አሏህን ትፈራለች፤ ባሏ በሚኖርበት ጊዜም ሆነ በማይኖርበት ጊዜ ትዳሯን ታከብራለች።
የባል ምርጫ በተመለከተ ደግሞ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡ ‹‹ባህሪው እና ሃይማኖቱ የወደዳችሁለት ሰው በመጣ ጊዜ ሴት ልጃችሁን ወይም በእናንተ ስር ያሉ ሴት ዘመዶቻችሁን ዳሩለት። ይህን ባታደርጉ ምድር ላይ ፈተና ይሆናል፤ ክፋትም ይስፋፋል።›› (ኢብንማጃ 1967) ሰለፎች (ቀደምቶች) እንዲህ ይሉ ነበር፡ ‹‹ሴት ልጃችሁን ልትድሩ ባሰባችሁ ጊዜ ሃይማኖቱን አጥብቆ ለያዘው ወንድ ዳሯት። በወደዳት ጊዜ ያከብራታል። በተከፋባት ጊዜ ደግሞ ያለ አግባብ አይበድላትም።››
የስነልቦና እርካታ
የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡ ‹‹ነፍሶች ልክ እንደ ምልምል ወታደሮች ናቸው። ባህሪያቸው የሚገጥም አንዳቸው ወደ አንዳቸው ይዘነበላሉ። ባህሪያቸው የማይገጥም ደግሞ ይለያያሉ።›› (ቡኻሪ 3336 ፣ ሙስሊም 2638) ይህ የሚያመለክተው ሁለቱ ጥንዶች ደስተኛ የትዳር ህይወታቸው ይቀጥል ዘንድ በስነልቦና የመስማማት እና የመዋደድ ጠቀሜታ ነው።
ለዚህም ነው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሴትን ለማግባት የፈለገ ሰው ‹‹እሷን ተመልከቱ፤ ሁለታችሁ መጣመራችሁ አይቀርምና›› በማለት ያዘዙት። (ትርሚዚ 1087) ከዚህ የምረዳው በመካከላቸው ያለው ፍቅር ይፀናል የሚለውን ነው። ይህ ሃሳብ የወንዱም የሴቷም መብት ነው።
ብቁነት
ብቁነት ማለት በትዳር አጋሮቹ መካከል ከቁሳዊ እና ከማህበራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በመካከላቸው ያለ መቀራረብ እና መስማማት ማለት ነው። አንዳንድ ሊቃውንቶች ይህ ጉዳይ ከግምት ውስጥ መግባት አለበት ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ሃይማኖቱ እና ባህሪ ብቻ በቂ ነው ይላሉ። ነገርግን በሁለቱ ጥንዶች መካከል ያለ ማህበራዊ ፣ ባህላዊ እና የገንዘብ አቅም ልዩነት የትዳርን ህይወት የሚፈትን እና ጎጆን የሚበትን ጉዳይ ነው።
መውደድ እና መቀበል
ሁለት ጥንዶች በደንብ ለመምረጥ ጥረት አድርገው ከተዋደዱ እና ከተቀበሉ በኋላ ጋብቻውን መፈፀም ያስፈልጋል። ጋብቻው የሚፈፀመው ያለ ማንም የቅርብ ሰዎች ግፊት ፣ ጎትጓችነት እና ማስገደድ መሆን አለበት።
እስልምና ለሚስት ፍትሃዊ ነው። ከባልየው መስማማት እና መቀበልን ቅድመ ሁኔታ አድርጎላታል። የአሏህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡ ‹‹አግብታ የፈታች ሴት ለትዳር አትሰጥም እሷ ካማከሩ በኋላ ቢሆን እንጅ። ድንግል ሴት ለትዳር አትሰጥም ፍቃዷን ከተቀበሉ በኋላ ቢሆን እንጅ። ሰዎችም ጠየቁ፡ ‹‹የአሏህ መልዕክተኛ ሆይ! ፈቃዷን እንዴት እናውቃለን አሉ። እሳቸውም ‹‹ዝምታዋ የመቀበሏ መልስ ነው›› አሉ።›› (ቡኻሪ 5136 ፣ ሙስሊም 1419) ኸንሳ ቢንት ኺዳም አል-አንሷሪ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፈችው አግብታ የፈታች ሆና ሳለ አባቷ ለትዳር ሰጣት። እሷም ትዳሩን ጠልታው ወደ አሏህ መልዕክተኛ ሄደች። እሳቸውም ጋብቻው ተቀባይነት የለውም አሉ። (ቡኻሪ 5138)