መማርዎን ይቀጥሉ

ሎግ ኢን አላደረክም
መማር ለመጀመር፣ እድገትን ለመከታተል፣ ነጥቦችን ለመሰብሰብ እና ወደ ውድድር ለመግባት አሁኑኑ በታ ፕላትፎርም ይመዝገቡ፡ ከተመዘገቡ በኋላ ለሚማሯቸው ርዕሶች የኤሌክትሮኒክስ ሰርተፍኬት ይደርስዎታል።

የአሁኑ ክፍል ::ሞዴል

ትምህርት የሶላት ትርጉም እና ደረጃው

ሶላት በእስልምና ትልቅ ደረጃ ያለው ሲሆን ይህም ከታላላቅ ምሰሶዎቹ አንዱ እና በሙስሊም ህይወት ውስጥ አስፈላጊ ምሰሶ ነው.በዚህ ትምህርት ስለ ጸሎት ትርጉም፣ ደረጃው እና መልካም ባህሪያቱ ትማራለህ።

  • የሶላትን ትርጉም ማወቅ።
  • ሶላት በእስልምና ያለውን ደረጃ ማወቅ።
  • የሶላት ትሩፋት እና አስፈላጊነት ማወቅ።

የሠላት መሰረታዊ ትርጉሙ

የሠላት መሰረታዊ ትርጉሙ፡ መማፀን ወይም መለመን ሲሆን፣ ባሪያን ከፈጣሪው ጋር የምታገናኝ መስመር ነች፡፡ በውስጧ ወሳኝ የሆኑ የባርነት መገለጫዎችን አቅፋለች፡፡ ወደ አላህ መሸሽና በርሱ መታገዝን አዝላለች፡፡ በሠላት ውስጥ ባሪያው ጌታውን ይለምናል፣ በሚስጥር ያወራል፣ ያወሳዋል፣ ነፍሱ ትጸዳለች፣ ባሪያው እውነተኛ ማንነቱን ያስታውስበታል፣ በውስጧ እየኖረባት ያለችውን የዱንያን ትክክለኛ ገጽታ ይገነዘባል፡፡ የዚህች ዓይነቷ ሠላት፣ በሪያው በአላህ ህግጋትና ድንጋጌ ላይ ጽናት እንዲኖረው፣ ከግፍ፣ ከዝሙትና ከአመፀኝነት እንዲርቅ ታደርገዋለች፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡ - «ሠላትንም ደንቡን ጠብቀህ ስገድ፤ ሠላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና፡፡» ይላል፡፡ (አል አንከቡት 45)

የሠላት ደረጃ

ሠላት ከአካላዊ አምልኮዎች ታላቋና ደረጇም የላቃ ነው፡፡ ቀልብን፣ አዕምሮንና ምላስን በአንድነት የሚያሳትፍ አምልኮ ነው፡፡ የሠላት አንገብጋቢነትን ከብዙ አቅጣጫ መመልከት ይቻላል፡፡ ከነዚህም

1 ከኢስላም ማዕዘናት መካከል ሁለተኛው ማዕዘን ነው፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ)፡- «ኢስላም በአምስት መሰረታዊ ማዕዘናት ላይ ተገነባ፡፡ -ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚገዙት አምላክ የለም፣ ሙሐመድ የአላህ መልክተኛ ናቸው ብሎ መመስከር፣ ሠላትን ማቋቋም፣….» ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 8 /ሙስሊም 16) የአንድ ግንባታ ማዕዘን ወይም ምሰሶ፣ ያለርሱ ግንባታው የማይቆምበት መሰረቱ ማለት ነው፡፡

2 ሸሪዓዊ መረጃዎች፣ በሙስሊሞችና በካሃዲያን መካከል መለያ ነጥብ ያደረጉት ሠላትን ማቋቋምን ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «በአንድ ሰውና በክህደት መሐከል ያለው ነገር ሠላትን መተው ነው፡፡» ብለዋል፡፡(ሙስሊም 82) «በእኛና በእነርሱ መሐከል ያለው ኪዳን ሠላት ነው፡፡ እርሷን የተወ በርግጥ ክዷል፡፡» ብለዋል፡፡ (አል ቲርሚዚ 2621/ አል ነሳኢ 463)

3 አላህ (ሱ.ወ) ሠላትን በማንኛውም ሁኔታ ላይ ሆኖ እንዲተገበር አዟል፡፡ በመንገደኛነት፣ በነዋሪነት፣ በሰላም፣ በጦርነት፣ በጤንነት፣ በህመምም ላይ ሆኖም ሁሉ ይተገበራል፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- «በሰላቶች ተጠባበቁ» ይላል፡፡ (አልበቀራ 238) ምዕመናን ባሮቹን ደግሞ፡- «እነዚያም እነሱ በስግደቶቻቸው ላይ የሚጠባበቁ የኾኑት፡፡» በማለት ይገልጻቸዋል፡ (አል ሙእሚኑን 9)

የሠላት ትሩፋት

የሠላትን ትሩፋት በማስመልከት በርካታ የቁርኣንና የሐዲስ ማስረጃዎች ተላልፈዋል፡፡ ከነሱም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

1 ሠላት ወንጀሎችን ታብሳለች፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡ - «አምስት ሠላቶችና ከጁምዓ እስከ ጁምዓ ትላልቅ ወንጀሎች እስካልተጣሱ ድረስ በመካከላቸው የሚፈፀሙትን ወንጀሎች ያብሳሉ፡፡» ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 233/ አል ቲርሚዚ 214)

2 ሠላት፣ለአንድ ሙስሊም በመላው ሕይወቱ የምታበራለት ብርሃኑ ናት፡፡ በመልካም ነገር ላይ ታግዘዋለች፡፡ ከመጥፎ ነገሮች ታርቃዋለች፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡ - «ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና፡፡» ይላል፡፡ (አል አንከቡት 45) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «ሠላት ብርሃን ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 223)

3 ሠላት፣ የትንሳኤ ቀን ባሪያው በመጀመሪያ የሚገመገምባት ጉዳይ ናት፡፡ እርሷ ካማረችና ተቀባይነት ካገኘች፣ የተቀረው ስራ ተቀባይነት ያገኛል፡፡ እርሷ ተመላሽ ከሆነች የተቀሩት ስራዎችም ተመላሽ ይሆናሉ፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «የትንሳኤ ቀን ባሪያው በመጀመሪያ የሚገመገምበት ነገር ሠላት ነው፡፡ እርሷ ካማረች የተቀሩት ስራዎቹ ያምራሉ፡፡ እርሷ ከተበላሸች የተቀሩት ስራዎችም ይበላሻሉ፡፡» ብለዋል፡፡ (አል ሙዕጀሙል አውሰጥ ሊጠበራኒ 1859)

ሙእሚን በጣም የሚረካበት ቆይታ፣ በሠላት ውስጥ ጌታውን ሲያናግር ነው፡፡ በዚህን ጊዜ፣ መንፈሳዊ እረፍትን፣ መረጋጋትናና አጫዋችን ያገኛል፡፡

ሠላት ለነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ታላቋ የዓይን ማረፊያ ነበረች፡፡ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) የህንኑ ሲገልጹ፡-«የዓይኔ መርጊያ በሰላት ውስጥ ተደርጎልኛል፡፡»ይላሉ፡፡ (አል ነሳኢ 3940)

ሶላት የነቢዩ ማረፊያ ናት

ነቢዩ ሰ/ዐ/ወ/ ወደ ሠላት ለሚጣራው ሙኣዚናቸው ቢላል፡- «ቢላል ሆይ በርሷ አሳርፈን» ይሉ ነበር፡፡ (አቡ ዳውድ 4985)

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ የሆነ ጉዳይ ካሳሰባቸው ወይም ካጨናነቃቸው ወደ ሰላት ይሸሹ ነበር፡፡ (አቡ ዳውድ 1319)

ትምህርቱን አጠናቅቀሃል


ፈተና ጀምር