የአሁኑ ክፍል ::ሞዴል
ትምህርት በቀደር ማመን
በአላህ ውሳኔ የማመን ትርጓሜ
በአላህ ውሳኔ የማመን ትርጓሜ ማንኛውም መልካምም ሆነ መጥፎ ነገር የሚከሰተው በአላህ ውሳኔና ፍርድ እንደሆነ በቁርጠኝነት ማረጋገጥ ነው፡፡ እርሱ ያሻውን ሰሪ ነው፡፡ በእርሱ ፍላጎት እንጂ የሚሆን አንድም ነገር የለም፡፡ ከሱ መሻት የሚወጣ ነገርም የለም፡፡ በዓለም ውስጥ ከርሱ ውሳኔ የሚወጣ ነገር የለም፡፡ ከርሱ ማዘጋጀት ወይም ማስተናበር ባሻገር የሚከሰትም ነገር የለም፡፡ ከዚህም ጋር ትዕዛዛትን እንዲፈፅሙ ባሮቹን አዟል፡፡ ክልከላዎችንም ከልክሏቸዋል፡፡ ለሚሰሯቸው ስራዎቻቸውም የመምረጥ ነጻነት ሰጥቷቸዋል፡፡ አይገደዱም፡፡ ስራቸው የሚከሰተው እንደ ችሎታቸውና እንደ ፍላጎታቸው ነው፡፡ አላህ እነሱንም ችሎታቸውንም የፈጠረ እሱ ነው፡፡ በእዝነቱ ያሻውን ያቀናል፡፡ በጥበቡ ያሻውን ያጠማል፡፡ እርሱ በሚሰራው አይጠየቅም እነርሱ ተጠያቂ ናቸው፡፡
የቀደር ትርጉም
አል-ቃዳር፡- አላህ ያለፈውን ነገር ሁሉ ወሰነ፣ እነሱ በሚታወቁ ጊዜያት እና በተወሰኑ ባህሪያት እንደሚፈጸሙ አወቀ፤ይህንንም ጻፋ፣ እንዲሁን ፈለጋ፣ ፈጠራም። ለርሱ በወሰነው መሠረት ይሆናል።
በአላህ ውሳኔ ማመን ግዴታ ነው ከኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱ ማዕዘን ነው፡፡ ይኸው እውነታ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጂብሪል ሰለ ኢማን ጠይቋቸው በሰጡት ምላሽ ላይ ተዘክሯል፡ - « በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመጻሕፍቱ፣ በመልዕክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀንና በአላህ ውሳኔ በክፉውም በደጉም ልታምን ነው፡፡» (ሙስሊም 8)
በአላህ ውሳኔ ማመን ምንን ያካትታል?
በአላህ ውሳኔ ማመን አራት ዋና ዋና ጉዳዮችን ያካትታል
1 እውቀት
አላህ (ሱ.ወ) በጥቅሉም ሆነ በዝርዝር ስለ ሁሉ ነገር ያውቃል ብሎ ማመን፡፡ እነሆ እርሱ ፍጡራን በሙሉ በርግጥ ከመፈጠራቸው በፊት ያውቃቸዋል፡፡ ሲሳያቸውን፣ ቆይታቸውን፣ ንግግራቸውንና ስራዎቻቸውን አስቀድሞ አውቆታል፡፡ ሁሉንም እንቅስቃሲያቸውንና መርጊያቸውን፣ ሚስጥራቸውንና ይፋቸውን ያውቃል፡፡ ከነርሱ ውስጥ ማናቸው የጀነት ጓዶች እንደሆኑና ማናቸው የእሳት ጓዶች እንደሆኑ አስቀድሞ ያውቃል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እርሱ አላህ ነው፡፡ ያ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ ሩቁንና ቅርቡን ዐዋቂ የኾነ ነው፡፡» (አል ሐሽር 22)
2 መጻፍ
አላህ(ሱ.ወ) ተግባራትን ሁሉ አስቀድሞ በለውሕ አል- መሕፉዝ ላይ አስፍሯቸዋል። ስለዚህ ማስረጃ የሚሆነው የሚከተለው አላህ (ሱ.ወ) ቃል ነው።‹‹ በምድርም በነፍሳችሁም መከራ(ማንንም) አትነካም ስንፈጥራት በፊት በመጽሐፍ የተመዘገበች ብትኾን እንጂ።ይህ በአላህ ላይ ገር ነው (አል ሐዲድ፡22) ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፦‹‹ አላህ የፍጡራንን ችሮታ ሰማያትንና ምድርን ከመፍጠሩ ሃምሳ ሺህ አመታት በፊት ጽፏል።››(ሙስሊም 2653)
3 መሻት
እርሷን የሚያስተጓጉላት ምንም ነገር በሌላት፣ ተፈጻሚ በሆነችው በአላህ መሻት እና ምንም በማይሳነው በአላህ ችሎታ ማመን፡፡ ማናቸውም ክስተት የሚከሰተው በአላህ መሻትና ችሎታ ነው፡፡ እርሱ የሻው ይሆናል እርሱ ያልሻው አይሆንም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- « የዓለማት ጌታ አላህ ካልሻም አትሹም፡፡» (አል ተክዊር 29)
4 መፍጠር
ማናቸውንም ነገር የሚያስገኘውና የሚያስከስተው ወይም የሚፈጥረው አላህ (ሱ.ወ) መሆኑን ማመን፡፡ እርሱ ብቸኛ ፈጣሪ ነው፡፡ ከርሱ ሌላ ያለ ነገር ሁሉ ፍጡር ነው፡፡ እርሱ በሁሉ ነገር ላይ ቻይ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ነገሩንም ሁሉ የፈጠረውና በትክክልም ያዘጋጀው ነው፡፡» (አል ፉርቃን 2)
የሰው ልጅ ምርጫ፣ ችሎታና ፍላጎት አለው፡፡
በአላህ ውሳኔ ማመን የሰው ልጅ በምርጫው በሚፈጽማቸው ተግባሮቹ ላይ ፍላጎትና ችሎታ አለው ከማለት ጋር አይቃረንም፤ አይጋጭም፡፡ ምክንያቱም የእስላማዊ ድንጋጌና ነባራዊ ተጨባጭ ክስተት ይህንን ለርሱ የሚያረጋግጡና የሚያጸድቁ ናቸው፡፡
ከእስላማዊ ድንጋጌ አንጻር አላህ (ሱ.ወ) መሻትን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፡- «ይህ የተረጋገጠው ቀን ነው፡፡ የሻም ሰው ወደ ጌታው መመለስን ይይዛል፡፡» (አል ነበእ 39) ችሎታን በማስመልከትም አላህ እንዲህ ብሏል፡- «አላህ ነፍስን ከችሎታዋ በላይ አያስገድዳትም፡፡ ለርስዋ የሰራችው አላት፡፡ በርስዋም ላይ ያፈራቺው (ኀጢኣት) አለባት፡፡» (አል በቀራ 286)
ከነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ደግሞ ማንኛውም ሰው ችሎታና መሻት እንዳለውና በነርሱም የሚሰራውን እንደሚሰራ፣ የሚተወውንም እንደሚተው ያውቃል፡፡ እንደመራመድና መሰል እንቅስቃሴዎች ያሉ በፍላጎቱ የሚከሰቱትን፣ እንደመንቀጥቀጥና እንደ ድንገተኛ መውደቅ ያሉ ያለፍላጎቱ ከሚፈጸሙት ለይቶ ያውቃል፡፡ ነገር ግን የፍጡር መሻትና መቻል በአላህ መሻትና ችሎታ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከናንተ ቀጥተኛ መኾንን ለሻ ሰው (መገሰጫ ነው) ፡፡ የዓለማት ጌታ አላህ ካልሻም አትሹም፡፡» (አል ተክዊር 28-29) በአንቀጹ ላይ እንደምንመለከተው መጀመሪያ የሰው ልጅን መሻት አጸደቀ፤ ከዚያም በአላህ መሻት ውስጥ የሚካተት እንደሆነ አሳሰበ፡ ምክንያቱም ፍጥረተ- ዓለሙ በጠቅላላ የአላህ ይዞታ ነው፡፡ በርሱ ይዞታ ውስጥ ደግሞ ከርሱ ዕወቀትና መሻት ውጭ የሚሆን ነገር አይኖርም፡፡
የግዳጅና ኃላፊነት፣ የትዕዛዝን የክልከላ ተያያዥነታቸው ከሰው ልጅ ችሎታና ምርጫው ጋር ነው፡፡ አንድ መልካም ሰሪ ቀናውን ጎዳና የመረጠ በመሆኑ ይመነዳል፡፡ መጥፎ ሰሪ ደግሞ እኩይ የሆነን የጥመት መንገድ በመምረጡ ይቀጣል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) የምንችለውን እንጂ አላስገደደንም፡፡ በመሆኑም አላህ በርሱ ውሳኔ በማመካኘት እርሱን ማምለክ መተውን ከአንድም ሰው አይቀበልም፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሰው ልጅ ከማመጹ በፊት አላህ አውቆ የወሰነው ምን እንደሆነ አያውቅም፡፡ አላህ ደግሞ ችሎታና የመምረጥ ነጻነት ሰጥቶታል፡፡ የመልካምና የመጥፎን ጎዳና ነጣጥሎ አብራርቶለታል፡፡ በመሆኑም ካመጸ፣ አመጽን ለአላህ ታዛዠ ከመሆን በላጭ አድርጎ የመረጠው እራሱ ነው፡፡ በአመጸኛነቱ የሚያገኘውን ቅጣት የመሸከም ግዴታ አለበት፡፡
በአላህ ውሳኔ የማመን ጥቅም ወይም ፍሬ
በአላህ ውሳኔ ማመን በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡
1 በአላህ ውሳኔ ማመን በዚህ የሕይወት ቆይታ ንቁ ሆኖ፣ አላህ የሚወደውን በመፈፀሙ እንዲጥርና እንዲተጋ ከሚያደርጉ ነገሮች ዋነኛውና ትልቁ ነገር ነው፡፡
ምእመናን በአላህ ላይ ከመመካታቸው ጎን ለጎን የክስተት ሰበቦችን እንዲጠቀሙ ታዘዋል፡፡ ኢማን ማለት ደግሞ በአላህ ፍቃድ እንጂ የክስተት ሰበቦች ውጤት ሊያስገኙ እንደማይችሉ እርግጠኛ መሆን ነው፡፡ ምክንያቱም የክስተት ሰበቦችን የፈጠረው አላህ ነው፡፡ ውጤታቸውንም የፈጠረውም እሱ ነው፡፡ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- «በሚጠቅምህ ነገር ላይ ታታሪ ሁን፡፡ በአላህ ታገዝ፡፡ አትሳነፍ፡፡ የሆነ (መሰናክል) ነገር ቢገጥምህ እንዲህ እንዲህ ባደረግ ኖሮ እንዲህ እንዲህ ይሆን ነበር አትበል፡፡ ነገር ግን አላህ ወሰነ ያሻውንም ፈፀመ በል፡፡ እንዲህ ቢሆን ኖሮ ማለት የሸይጣንን በር ትከፍታለች፡፡» (ሙስሊም 2664) አንዳንድ ሰዎች ነገሮች ከተወሰኑ መሥራት አያስፈልግም ብለው ሲያስቡ ነብዩ (ሶ.ዐ.ወ) ስህተት መሆኑን አስረድተዋል። እሳቸውም እንዲህ አሉ፡- (ስሩ ሁሉም ለተፈጠረ ነገር ገር ነው)። ከዚያም እንዲህ ብለዋል፡- { ያ እሱ የሰጠ፣ አላህን የፈራ፣ እውነተኛይቱን ቃል ያመነ ሰው፡}እስከ {ለችግርም እናገራዋለን።} (አል-ለይል፡ 10)። (ቡኻሪ 4949፣ ሙስሊም 2647)።
2 የሰው ልጅ የነፍሱን ልክ ማወቅ አለበት፡፡
ሊኮራም ሊኮፈስም አይገባም፡፡ ምክንያቱም እሱ በአላህ የተወሰነውን ነገርና ወደፊት የሚከሰተውን ክስተት ማወቅ የማይችል ደካማ ፍጡር ነው፡፡ በመሆኑም የሰው ልጅ ምንጊዜም በደካማነቱና ወደ ፈጣሪው ከጃይ መሆኑን ማመን አለበት፡፡ የሰው ልጅ በተፈጥሮው መልካም ነገር ሲገጥመው ይኮራል በርሱም ይታለላል፡፡ መጥፎ ነገርና አደጋ ሲያጋጥመው ደግሞ ይበሳጫል፤ ይተክዛል፡፡ እናም የሰው ልጅን በአላህ ውሳኔ ከማመን በስተቀር መልካም ነገር ሲገጥመው ከመኮፈስና ድንበር ከማለፍ፣ እንዲሁም መጥፎ ነገር ሲገጥመው ከማዘንና ከመተከዝ ሊታደገው የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡ ማናቸውም የተከሰቱና የሚከሰቱ ነገሮች የአላህ ውሳኔ የተላለፈባቸውና አላህ አስቀድሞ ያወቃቸው ናቸው፡፡
3 በአላህ ውሳኔ ማመን ውግዝ ለሆነው ምቀኝነት እልባት ይሰጣል፡፡
አንድ ሙእሚን አላህ ከችሮታው በሰጣቸው ነገር ሰዎችን አይመቀኝም፡፡ ለነርሱ የለገሳቸውና ይህንን ነገር የወሰነላቸው አላህ (ሱ.ወ) ነው፡፡ እናም ሙእሚን ሌሎችን ሲመቀኝ በአላህ ውሳኔና ፍርድ ላይ እያመጸ መሆኑን ወይም ውሳኔውን እየተቃወመ እንደሆነ ያውቃል፤ ስለሆነም አይመቀኝም፡፡
4 በአላህ ውሳኔ ማመን በልብ ውስጥ ችግሮችን ለመጋፈጥ ጀግንነትን ይፈጥራል፡፡
ቁርጠኝነትንም ያጠናክራል፡፡ ምክንያቱ፣ በአላህ ውሳኔ ማመን የዱንያ ቆይታ (አጀል) ሲሳይ በአላህ የተወሰነ እንደሆነና የሰው ልጅን የሚያጋጥመው የተጻፈው ነገር ብቻ መሆኑን እርግጠኛ እንዲሆኑ ስለሚያደርግ ነው፡፡
-5 በአላህ ውሳኔ ማመን በሙእሚን ነፍስ ውስጥ የተለያዩ የኢማን ጭብጦችን ይተክላል፡፡
እርሱ ምንጊዜም እገዛ የሚሻው ከአላህ ብቻ ነው፡፡ የክስተት ሰበቦችን ከመፈፀሙም ጋር የሚንተራሰውና የሚመካው በአላህ ላይ ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም ምንጊዜም ጌታውን ከጃይ ይሆናል፡፡ በጽናት ላይ እንዲያበረታው ከርሱ እገዛን ይፈልጋል፡፡
6 በአላህ ውሳኔ ማመን የመንፈስ እርጋታን ይፈጥራል፡፡
ሙእሚን፣፣ የደረሰበት ነገር መጀመሪያውኑ ሊስተው እንዳልነበረ፣ የሳተውም ነገር መጀመሪያውኑ ሊያገኘው እንዳልነበረ ያውቃል፡፡